ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 37:10-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልህ።

11. እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12. የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን?

13. የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”

14. ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።

15. ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

16. “በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል።

17. አቤቱ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብል፤ አድምጥም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈት፤ ተመልከትም። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።

18. “እግዚአብሔር ሆይ፤ በርግጥ የአሦር ነገሥታት እነዚህን ሕዝቦች፣ ምድራቸውንም ሁሉ ባድማ አድርገዋል።

19. አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና።

20. አሁንም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”

21. ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣

22. እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ንቃሃለች፣ አፊዛብሃለች፤የኢየሩሳሌም ልጅ፣አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።

23. የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?ድምፅህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፣ዐይንህን በትዕቢት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እኮ!

24. በመልእክተኞችህ በኩል፣በጌታ ላይ ብዙ የስድብ ቃል ተናገርህ፤እንዲህም አልህ፤“በሰረገሎቼ ብዛት፣የተራሮችንም ከፍታ፣የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤ረጃጅም ዝግባዎችን፣የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤እጅግ ወደራቁት ከፍታዎች፣እጅግ ውብ ወደ ሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ፤

25. በባዕድ ምድር ጒድጓዶችን ቈፈርሁ፤ከዚያም ውሃ ጠጣሁ።የግብፅን ምንጮች ሁሉ፣በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።”

26. “ ‘ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣ጥንትም እንዳቀድሁት፣አልሰማህምን?አሁን ደግሞ እንዲፈጸም አደረግሁት፤አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የድንጋይክምር አደረግሃቸው።

27. የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጦአል፤ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣እንደ ለጋ ቡቃያ፣በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።

28. “ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣መምጣት መሄድህ ምን ጊዜ እንደሆነ፣በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደም ትነሣሣ ዐውቃለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 37