ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 37:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ።

2. የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ኤልያቄምንና ጸሓፊውን ሳምናስን እንዲሁም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ሁሉም ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው።

3. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ሕፃናት ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኖአል።

4. ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።”

5. የንጉሡ የሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤

6. ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር።

7. እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”

8. የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቆ መሄዱን ሲሰማ፣ ከነበረበት ተመለሰ፤ ንጉሡም የልብናን ከተማ ሲወጋ አገኘው።

9. ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤

10. “ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልህ።

11. እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12. የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 37