ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 36:8-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. “ ‘አሁን፣ ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተደራደር፤ የሚቀመጡባቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።

9. እንግዲህ በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች የምትተማመን ከሆነ፣ ከጌታዬ መኰንንኖች አንዱን ዝቅተኛ መኰንን እንዴት መመለስ ይቻልሃል?

10. ደግሞስ ይህን ምድር ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይመስልሃልን? እግዚአብሔር ራሱ በዚህ አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋው ነግሮኛል።’ ”

11. ኤልያቄምና ሳምናስ እንዲሁም ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እባክህ በምናውቀው በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚያውቀው በዕብራይስጥ ቋንቋ አትናገረን” አሉት።

12. ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ነገሮች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኩስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው።

13. የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ቋንቋ በታላቅ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።

14. ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ እርሱ ሊያድናችሁም አይችልም።

15. “እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር አትሰጥም’ እያለ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።’

16. “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ከእኔ ጋር ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤

17. ይኸውም መጥቼ የእህልና የአዲስ ወይን ጠጅ ምድር ወደሆነችው፣ የእንጀራና የወይን ምድር ወደሆነችው፣ ምድራችሁን ወደ ምትመስል አገር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።’

18. “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ያድነናል’ በማለት አያታልላችሁ”፤ ለመሆኑ፣ እስካሁን ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያዳነ የየትኛው ሕዝብ አምላክ ነው።

19. የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክትስ የት አሉ? እነዚህ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 36