ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 36:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ቋንቋ በታላቅ ድምፅ እንዲህ አለ፤ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።

14. ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ እርሱ ሊያድናችሁም አይችልም።

15. “እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር አትሰጥም’ እያለ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።’

16. “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ከእኔ ጋር ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤

17. ይኸውም መጥቼ የእህልና የአዲስ ወይን ጠጅ ምድር ወደሆነችው፣ የእንጀራና የወይን ምድር ወደሆነችው፣ ምድራችሁን ወደ ምትመስል አገር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።’

18. “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ያድነናል’ በማለት አያታልላችሁ”፤ ለመሆኑ፣ እስካሁን ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያዳነ የየትኛው ሕዝብ አምላክ ነው።

19. የሐማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክትስ የት አሉ? እነዚህ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?

20. ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ፣ ምድሩን ከእጄ ለማዳን የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ፣ እግዚአብሔር እንዴት ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያድን ይችላል?”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 36