ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 36:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው።

2. የአሦርም ንጉሥ የጦር አዛዡን ከብዙ ሰራዊት ጋር ከለኪሶ፣ ንጉሡ ሕዝቅያስ ወዳለበት፣ ወደ ኢየሩሳሌም ላከው። የጦር አዛዡም ወደ ልብስ አጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ፣ በላይኛው ኵሬ ቦይ አጠገብ ደርሶ ቆመ፤

3. የቤተ መንግሥቱ አስተዳዳሪ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።

4. የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤“ ‘ታላቁ ንጉሥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው?

5. የጦር ስልትና ጠንካራ ሰራዊት አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ፍሬ ቢስ ቃል ብቻ ትናገራለህ። ለመሆኑ፣ በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?

6. እነሆ፤ ሰው ሲመረ ኰዘው እጅ ወግቶ በሚያቈስለው፣ በተሰነጠቀ ሸምበቆ በግብፅ ተማምነሃል፤ የግብፅ ንጉሥ፣ ፈርዖንም ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።

7. ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የእርሱንማ ማምለኪያ ኰረብቶችና መሠዊያዎች ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ እንዲህ ባለው በአንዱ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን?

8. “ ‘አሁን፣ ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተደራደር፤ የሚቀመጡባቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።

9. እንግዲህ በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች የምትተማመን ከሆነ፣ ከጌታዬ መኰንንኖች አንዱን ዝቅተኛ መኰንን እንዴት መመለስ ይቻልሃል?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 36