ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 35:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤እንደ አደይም ያብባል።

2. በደስታና በዝማሬ ሐሤት ያደርጋል፤የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤የቀርሜሎስንና የሳሮንን ግርማ ይለብሳል።የአምላካችንን ታላቅ ግርማ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ።

3. የደከሙትን እጆች አበርቱ፤የላሉትንም ጒልበቶች አጽኑ፤

4. የሚፈራ ልብ ላላቸው እንዲህ በሉ፤“በርቱ፤ አትፍሩ፤አምላካችሁ ይመጣል፤ሊበቀል ይመጣል፤እርሱም ብድራቱን ይዞ፣ሊያድናችሁ ይመጣል።”

5. በዚያን ጊዜም የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ፤የደንቈሮም ጆሮዎች ይከፈታሉ።

6. አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል፤ውሃ ከበረሓ ይወጣል፤ምንጮችም ከምድረ በዳ ይፈልቃሉ።

7. ንዳዳማው ምድር ኵሬ ይሆናል፤የተጠማው መሬት ውሃ ያመነጫል።ቀበሮዎች በተኙባቸው ጒድጓዶች፣ሣር፣ ሸምበቆና ደንገል ይበቅልበታል።

8. በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤“የተቀደሰ መንገድ” ተብሎ ይጠራል።የረከሱ አይሄዱበትም፤በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል።ገራገሮችም ከመንገዱ አይስቱም።

9. አንበሳ አይኖርበትም፤ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም፤እነዚህማ በዚያ ስፍራ አይገኙም፤የዳኑት ብቻ በዚያ ይሄዳሉ፤

10. እግዚአብሔር የዋጃቸው ይመለሳሉ።እየዘመሩ ወደ ጽዮን ይገባሉ፤ዘላለማዊ ደስታን እንደ አክሊል ይቀዳጁታል፤ፍሥሓና ሐሤት ያገኛሉ፤ሐዘንና ትካዜ ከዚያ ይሸሻሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 35