ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 24:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ጨርሶም ትበዘበዛለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።

4. ምድር ትደርቃለች፤ ትረግፋለች፤ዓለም ትዝላለች፤ ትረግፋለች፤የምድርም መሳፍንት ይዝላሉ።

5. ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ሕግን ጥሰዋል፤ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።

6. ስለዚህ ርግማን ምድርን ትበላለች፤ሕዝቦቿም ስለ በደላቸው ይቀጣሉ፤ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ተቃጥለዋል፤በጣም ጥቂት የሆኑት ቀርተዋል።

7. አዲሱ የወይን ጠጅ አለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ።

8. የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ደስ የሚያሰኘውም በገና እረጭ አለ።

9. ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤መጠጡም ለሚጠጡት ይመራል።

10. የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ።

11. በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቶአል።

12. ከተማዪቱ ፈጽማ ፈርሳለች፤በሮቿም ደቀው ወድቀዋል።

13. የወይራ ዛፍ ሲመታ፣የወይንም ዘለላ ሲቈረጥ ቃርሚያ እንደሚቀር ሁሉ፣በምድሪቱ ላይ፣በሕዝቦችም ላይ እንዲሁ ይሆናል።

14. ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤ በደስታም ይጮኻሉ፤ከምዕራብም የእግዚአብሔርን ክብር ያስተጋባሉ።

15. ስለዚህ በምሥራቅ ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ፤ከባሕር ደሴቶችም፣የእስራኤልን አምላክ፣ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ አድርጉ።

16. “ለጻድቁ ክብር ይሁን” የሚል ዝማሬ፣ከምድር ዳርቻ ሰማን፤እኔ ግን፣ “ከሳሁ፤ መነመንሁ፤ወዮልኝ!ከዳተኞች አሳልፈው ሰጡ፤ከዳተኞች በክሕደታቸው አሳልፈው ሰጡ” አልሁ።

17. በምድር የምትኖር ሕዝብ ሆይ፤ሽብር፣ ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቁሃል።

18. ከሽብር ድምፅ የሚሸሽ፣ወደ ጒድጓድ ይገባል፤ከጒድጓድ የወጣም፣በወጥመድ ይያዛል።የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፤የምድርም መሠረት ተናወጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 24