ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 19:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ግብፃውያንን አሳልፌ፣ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

5. የዐባይ ወንዝ ይቀንሳል፤ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።

6. መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤የግብፅ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም።ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤

7. እንዲሁም በዐባይ ዳር፣በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ።በዐባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።

8. ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤በዐባይ ወንዝ ላይ መንጠቆአቸውን የሚወረውሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤በውሃ ላይ መረባቸውን የሚጥሉ ሁሉ፣ጒልበታቸው ይዝላል።

9. የተነደፈ የተልባ እግር የሚፈትሉ፣የተባዘተ ጥጥ የሚሠሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቈርጣሉ።

10. ልብስ ሠሪዎች ያዝናሉ፤ደመወዝተኞችም ልባቸው ይሰበራል።

11. የጣኔዎስ አለቆች በጣም ሞኞች ናቸው፤የፈርዖን ጠቢባን ምክራቸው የማይረባ ነው፤ፈርዖንን፣ “እኔ ከጥበበኞች አንዱ ነኝ፤የጥንት ነገሥታትም ደቀ መዝሙር ነኝ”እንዴት ትሉታላችሁ?

12. የእናንተ ጠቢባን አሁን የት አሉ?የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርበግብፅ ላይ ያሰበውን ነገር፣እስቲ ያሳዩአችሁ፤ ያሳውቋችሁም።

13. የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤የሜምፊስ ሹማምት ተታለዋል፤የሕዝቧ ዋና ዋናዎች፣ግብፅን አስተዋታል።

14. እግዚአብሔር የድንዛዜን መንፈስ አፍሶባቸዋል፤ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ፣ግብፅንም በምታደርገው ነገር ሁሉእንድትንገዳገድ አደረጓት።

15. ራስም ይሁን ጅራት፣ የዘንባባ ዝንጣፊም ይሁን ደንገል፣ለግብፅ የሚያደርጉላት አንዳች ነገር የለም።

16. በዚያን ቀን ግብፃውያን እንደ ሴት ይሆናሉ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካነሣው ክንዱ የተነሣ በፍርሀት ይንቀጠቀጣሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 19