ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 13:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. በተራሮች ላይ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣የሚሰማውን ጩኸት አድምጡበመንግሥታትም መካከል፣እንደ ተጨናነቀ ሕዝብ ድምፅ የሆነውን ውካታ ስሙ!የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርሰራዊቱን ለጦርነት አሰልፎአል።

5. እግዚአብሔርና የቍጣው ጦር መሣሪያ፣ምድሪቱን በሙሉ ለማጥፋት፣ከሩቅ አገር፣ከሰማያትም ዳርቻ መጥተዋል።

6. የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና አልቅሱ፤ሁሉን ቻይ ከሆነ አምላክ ዘንድ ጥፋት ይመጣልና።

7. ስለዚህ እጆች ሁሉ ሽባ ይሆናሉ፤የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።

8. ሽብር ይይዛቸዋል፤ሥቃይና ጭንቀት ይደርስባቸዋል፤ምጥ እንደ ያዛት ሴት ያምጣሉ፤እርስ በርሳቸው በድንጋጤ ይተያያሉ፤ፊታቸውም በፍርሀት ቀይ ይሆናል።

9. እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ጨካኝ ነው፤ምድርን ባድማ ሊያደርጋት፣በውስጧም ያሉትን ኀጢአተኞች ሊያጠፋ፣ከመዓትና ከብርቱ ቍጣ ጋር ይመጣል።

10. የሰማይ ከዋክብትና ሰራዊታቸው፣ብርሃን አይሰጡም፤ፀሓይ ገና ከመውጣቷ ትጨልማለች፤ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

11. ዓለምን ስለ ክፋቷ፣ክፉዎችንም ስለ ኀጢአታቸው እቀጣለሁ፤የትዕቢተኞችን እብሪት እሽራለሁ፤የጨካኞችንም ጒራ አዋርዳለሁ።

12. ሰውን ከነጠረ ወርቅ ይልቅ ውድ፣ከኦፊርም ወርቅ ይበልጥ ብርቅ አደርጋለሁ።

13. ስለዚህ በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት፣ቍጣው በሚነድበት ቀን፣ሰማያትን እነቀንቃለሁ፤ምድርንም ከስፍራዋ አናውጣለሁ።

14. እንደሚታደን ሚዳቋ፣እረኛም እንደሌለው የበግ መንጋ፣እያንዳንዱ ወደ ወገኑ ይመለሳል፣እያንዳንዱም ወደ አገሩ ይሸሻል።

15. የተማረከ ሁሉ ይወጋል፤የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።

16. ዐይናቸው እያየ ሕፃናታቸው ይጨፈጨፋሉ፤ቤታቸው ይዘረፋል፤ ሚስቶቻቸው ይደፈራሉ።

17. እነሆ፤ ለብር ደንታ የሌላቸውን፣በወርቅም ደስ የማይሰኙትን፣ሜዶናውያንን አስነሣባቸዋለሁ።

18. ቀስታቸው ጐበዞችን ይፈጃል፤ሕፃናትን አይምሩም፤ዐይናቸውም ለልጆች አይራራም።

19. የመንግሥታት ዕንቍ፣የከለዳውያን ትምክሕት፣የሆነችውን ባቢሎንን፣ እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 13