ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 9:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. የእነርሱን መጥፋት በሚፈልጉ ወገኖች ላይ አደጋ ለመጣል አይሁድ በንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች ሁሉ ባሉት ከተሞቻቸው ተሰበሰቡ። የሌሎቹ አገር ዜጎች ሕዝብ ሁሉ ፈርተዋቸው ስለ ነበር፣ ማንም ሊደፍራቸው አልቻለም።

3. የየአውራጃው መኳንንት ሁሉ፣ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦች እንዲሁም የንጉሡ አስተዳዳሪዎች አይሁድን ረዷቸው፤ ይህን ያደረጉትም መርዶክዮስን ስለ ፈሩ ነበር።

4. መርዶክዮስ በቤተ መንግሥቱ ታዋቂ ሆነ፤ ዝናው በየአውራጃው ሁሉ ተሰማ፤ ኀይሉም እየበረታ ሄደ።

5. ስለዚህ አይሁድ ጠላቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ እየመቱ ገደሏቸው፤ አጠፏቸውም፤ በሚጠሏቸውም ላይ ደስ ያላቸውን አደረጉ።

6. አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰው ገደሉ፤ አጠፉም።

7. ፖርሻንዳታን፣ ደልፎንን፣ አስፓታን፣

8. ፖራታን፣ አዳልያን፣ አሪዳታን፣

9. ፓርማ ሽታን፣ አሪሳይን፣ አሪዳይንና ዋይዛታንም ገደሉ፤

10. እነዚህም የአይሁድ ጠላት የሆነው የሐመዳቱ ልጅ የሐማ ዐሥር ወንዶች ልጆች ነበሩ። በምርኮው ላይ ግን እጃቸውን አልዘረጉም።

11. በሱሳ ግንብ የተገደሉት ሰዎች ብዛት በዚያኑ ዕለት ለንጉሡ ተነገረው።

12. ንጉሡም ንግሥት አስቴርን፣ “አይሁድ በሱሳ ግንብ አምስት መቶ ሰውና ዐሥሩን የሐማ ልጆች ገድለዋል፤ አጥፍተዋልም። በተቀሩት በንጉሡ አውራጃዎችስ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትለምኚው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ የምትጠይቂውስ ምንድን ነው? ይፈቀድልሻል” አላት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 9