ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 3:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሥ ጠረክሲስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከሌሎቹም መኳንንት ሁሉ ከፍተኛውን ሥልጣን በመስጠት አከበረው።

2. ንጉሡ ስለ እርሱ ይህ እንዲደረግለት አዞ ስለ ነበር፣ በንጉሡ በር ያሉት የመንግሥቱ ሹማምት ሁሉ ለሐማ ተንበርክከው እጅ በመንሣት አክብሮታቸውን ይገልጡለት ነበር። መርዶክዮስ ግን ወድቆ አልሰገደለትም፤ አክብሮትም አላሳየውም።

3. ታዲያ በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፣ “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” ሲሉ ጠየቁት።

4. ይህንንም በየቀኑ ይነግሩት ነበር፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሮአቸው ስለ ነበር፣ የመርዶክዮስ ባሕርይ እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል ለማየት ሲሉ ይህንኑ ለሐማ ነገሩት።

5. ሐማም መርዶክዮስ ወድቆ እንዳልሰገደለትና እንዳላከበረው ሲያይ እጅግ ተቈጣ።

6. ይልቁንም መርዶክዮስ ከእነማን ወገን መሆኑን በተረዳ ጊዜ፣ መርዶክዮስን ብቻ መግደል እንደ ኢምንት ቈጠረው፤ ስለዚህ ሐማ በመላው የጠረክሲስ መንግሥት ውስጥ የሚገኙትንና የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ፈለገ።

7. ንጉሥ ጠረክሲስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር፣ ቀኑንና ወሩን ለመለየት ፉር የተባለ ዕጣ ሐማ ባለበት ጣሉ፤ ዕጣውም አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ላይ ወደቀ።

8. ከዚያም ሐማ ንጉሥ ጠረክሲስን እንዲህ አለው፤ “በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተሠራጭቶና ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ልማድ ያለውና የንጉሡንም ሕግ የማይታዘዝ ነው፤ ታዲያ ይህን ሕዝብ ዝም ማለቱ ለንጉሡ አይበጅም።

9. ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ እነርሱን ለማጥፋት ዐዋጅ ይውጣ፤ እኔም ይህን ተግባር ለሚፈጽሙ ሰዎች የሚውል ዐሥር ሺህ መክሊት ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት አስገባለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 3