ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 2:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. የንጉሡ ትእዛዝና ዐዋጅ በወጣ ጊዜ፣ ብዙ ልጃገረዶች ወደ ሱሳ ግንብ ተወስደው ለጠባቂው ለሄጌ ተሰጡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ተወስዳ፣ ለሴቶቹ ጠባቂ ለሄጌ በዐደራ ተሰጠች።

9. ልጃገረዲቱም ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች፤ እርሱም የውበት መንከባከቢያዋንና የተለየ ምግብ ወዲያውኑ ሰጣት። ከቤተ መንግሥቱ የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮችን በመመደብም እርሷንና ደንገጡሮቿን ምርጥ ወደ ሆነው የሴቶች መጠበቂያ አዛወረ።

10. መርዶክዮስ እንዳትናገር አዞአት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደሆነች አልገለጸችም።

11. መርዶክዮስም አስቴር እንዴት እንደሆነችና ምንስ እንዳጋጠማት ለማወቅ፣ በየዕለቱ በሴቶች መጠበቂያ አደባባይ አጠገብ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።

12. አንዲት ልጃገረድ ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ዘንድ ለመግባት ተራዋ ከመድረሱ በፊት ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ ልዩ ልዩ ሽቱ በመቀባትና በተለያዩ የፊት ቀለሞች በመዋብ ባጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ወር መቈየት ነበረባት፤

13. ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትገባውም በዚህ ሁኔታ ሲሆን፣ ሴቶቹ ከሚኖሩበት ስፍራ ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ስትሄድ፣ መውሰድ የምትፈልገው ማናቸውም ነገር ይሰጣት ነበር።

14. ሲመሽ ወደዚያው ትሄዳለች፤ ሲነጋም የቁባቶች ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሻአሽጋዝ ጥበቃ ሥር ወደሚገኘው ወደ ሌላው የሴቶች መጠበቂያ ቤት ትመለሳለች፤ ደስ የተሰኘባት ካልሆነችና በስሟም ካልጠራት ዳግመኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ አትገባም።

15. መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የአጎቱ የአቢካኢል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትሄድበት ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ልዩ ጥበቃ ቤት ኀላፊ የሆነው ሄጌ የነገራትን እንጂ፣ ሌላ ምንም አልጠየቀችም። አስቴር በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች።

16. በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት በተባለው በዐሥረኛው ወር ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ተወሰደች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 2