ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 2:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት አንዱ ነበር።

7. መርዶክዮስ አንዲት ሀደሳ የምትባል የአጎቱ ልጅ ነበረችው፤ አባትና እናት ስላልነበራት፣ ያሳደጋት እርሱ ነበር። አስቴር ተብላ የምትጠራው ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች። አባቷና እናቷ ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት።

8. የንጉሡ ትእዛዝና ዐዋጅ በወጣ ጊዜ፣ ብዙ ልጃገረዶች ወደ ሱሳ ግንብ ተወስደው ለጠባቂው ለሄጌ ተሰጡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ተወስዳ፣ ለሴቶቹ ጠባቂ ለሄጌ በዐደራ ተሰጠች።

9. ልጃገረዲቱም ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች፤ እርሱም የውበት መንከባከቢያዋንና የተለየ ምግብ ወዲያውኑ ሰጣት። ከቤተ መንግሥቱ የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮችን በመመደብም እርሷንና ደንገጡሮቿን ምርጥ ወደ ሆነው የሴቶች መጠበቂያ አዛወረ።

10. መርዶክዮስ እንዳትናገር አዞአት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደሆነች አልገለጸችም።

11. መርዶክዮስም አስቴር እንዴት እንደሆነችና ምንስ እንዳጋጠማት ለማወቅ፣ በየዕለቱ በሴቶች መጠበቂያ አደባባይ አጠገብ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።

12. አንዲት ልጃገረድ ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ዘንድ ለመግባት ተራዋ ከመድረሱ በፊት ስድስት ወር በከርቤ ዘይት፣ ስድስት ወር ደግሞ ልዩ ልዩ ሽቱ በመቀባትና በተለያዩ የፊት ቀለሞች በመዋብ ባጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ወር መቈየት ነበረባት፤

13. ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትገባውም በዚህ ሁኔታ ሲሆን፣ ሴቶቹ ከሚኖሩበት ስፍራ ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ስትሄድ፣ መውሰድ የምትፈልገው ማናቸውም ነገር ይሰጣት ነበር።

14. ሲመሽ ወደዚያው ትሄዳለች፤ ሲነጋም የቁባቶች ኀላፊ በሆነው በንጉሡ ጃንደረባ በሻአሽጋዝ ጥበቃ ሥር ወደሚገኘው ወደ ሌላው የሴቶች መጠበቂያ ቤት ትመለሳለች፤ ደስ የተሰኘባት ካልሆነችና በስሟም ካልጠራት ዳግመኛ ወደ ንጉሡ ዘንድ አትገባም።

15. መርዶክዮስ እንደ ልጁ አድርጎ ያሳደጋት የአጎቱ የአቢካኢል ልጅ አስቴር ወደ ንጉሡ ዘንድ የምትሄድበት ተራ በደረሰ ጊዜ የሴቶች ልዩ ጥበቃ ቤት ኀላፊ የሆነው ሄጌ የነገራትን እንጂ፣ ሌላ ምንም አልጠየቀችም። አስቴር በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች።

16. በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት በተባለው በዐሥረኛው ወር ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ተወሰደች።

17. በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት።

18. ንጉሡም ስለ አስቴር ክብር ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በዓሉም በየአውራጃዎቹ ሁሉ እንዲከበር ዐወጀ፤ በንጉሣዊ ልግስናውም ስጦታ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 2