ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 2:16-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ቴቤት በተባለው በዐሥረኛው ወር ወደ ንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ተወሰደች።

17. በዚህ ጊዜ ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት።

18. ንጉሡም ስለ አስቴር ክብር ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ በዓሉም በየአውራጃዎቹ ሁሉ እንዲከበር ዐወጀ፤ በንጉሣዊ ልግስናውም ስጦታ አደረገ።

19. ደናግሉ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰብስበው ሳለ፣ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር።

20. አስቴር ግን ልክ መርዶክዮስ እንደ ነገራት የማን ወገንና የየት አገር ሰው እንደሆነች ደብቃ ነበር፤ ይህ የሆነበት ምክንያት መርዶክዮስ በሚያሳድጋት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ፣ አሁንም ምክሩን ትከተል ስለ ነበር ነው።

21. መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ፣ በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አለቆች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፤ ንጉሥ ጠረክሲስንም ለመግደል ዶለቱ።

22. መርዶክዮስም አድማውን ስለ ደረሰበት፣ ለንግሥት አስቴር ገለጠላት፤ እርሷም ይህን ከመርዶክዮስ ማግኘቷን ለንጉሡ ገልጣ ነገረችው።

23. ነገሩ ሲጣራም እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ሁለቱም ሹማምት በስቅላት ሞት ተቀጡ። ይህ ሁሉ በንጉሡ ፊት በታሪክ መዝገብ ተጻፈ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 2