ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 1:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ንጉሡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ያህል እንዲያቀርቡለት የወይን ጠጅ አሳላፊዎቹን ሁሉ አዝዞ ስለ ነበረ፣ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ ተስተናጋጅ እንዲጠጣ ተፈቅዶለት ነበር።

9. ንግሥት አስጢንም በንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት እንደዚሁ ለሴቶች ግብዣ አድርጋ ነበር።

10. በሰባተኛው ቀን ንጉሥ ጠረክሲስ ከወይን ጠጁ የተነሣ ደስ ስለ ተሰኘ፣ አገልጋዮቹ የሆኑትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፣ ባዛንን፣ ሐርቦናን፣ ገበታን፣ ዘቶልያንን፣ ዜታርንና ከርከስን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤

11. ይኸውም ንግሥት አስጢን የደስ ደስ ያላት ነበረችና ውበቷ ለሕዝቡና ለመኳንንቱ እንዲታይ ዘውዷን ጭና ንጉሡ ፊት እንዲያመጧት ነበር።

12. አገልጋዮቹ የንጉሡን ትእዛዝ በነገሯት ጊዜ ግን፣ ንግሥት አስጢን መሄድ አልፈለገችም። ከዚያም ንጉሡ በጣም ተቈጣ፤ እጅግም ተናደደ።

13. ሕግንና ፍትሕን በተመለከተ የሊቃውንቱን ምክር መጠየቅ በንጉሥ ዘንድ የተለመደ ነበርና፣ ስለ ዘመናት ሁኔታ ዕውቀት ካላቸው ጠቢባን ጋር ተነጋገረበት፤

14. እነዚህ አርቄስዮስ፣ ሼታር፣ አድማታ፣ ተርሺሽ፣ ሜሬስ፣ ማሌሴዓር፣ ምሙካ የተባሉ ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መኳንንት በንጉሡ ዘንድ የተለየ ስፍራና በመንግሥቱም አመራር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ነበሩ።

15. ንጉሡም፣ “በጃንደረቦቹ በኩል የተላከባትን የንጉሥ ጠረክሲስን ትእዛዝ ስላልፈጸመች፣ በሕጉ መሠረት በንግሥት አስጢን ላይ ምን መደረግ አለበት?” ሲል ጠየቃቸው።

16. ከዚያም ምሙካ በንጉሡና በመኳንንቱ ፊት እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንግሥት አስጢን የበደለችው ንጉሡን ብቻ ሳይሆን፣ መኳንንቱን ሁሉና በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃዎች የሚኖሩትን ሕዝቦች ጭምር ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 1