ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 1:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ያሉትን አንድ መቶ ሃያ ሰባት አገሮች ይገዛ በነበረው በጠረክሲስ ዘመነ መንግሥት እንዲህ ሆነ፤

2. በዚያን ዘመን ንጉሡ ጠረክሲስ የገዛው በሱሳ ግንብ ባለው ንጉሣዊ ዙፋኑ ሆኖ ነበር።

3. እርሱም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለመኳንንቱና ለሹማምቱ ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ። በግብዣውም የፋርስና የሜዶን የጦር አዛዦች፣ መሳፍንትና የየአውራጃው መኳንንት ተገኝተው ነበር።

4. ለእነርሱም የመንግሥቱን ሰፊ ሀብት፣ የግርማውን ታላቅነትና ክብር አንድ መቶ ሰማንያ ቀን ሙሉ አሳያቸው።

5. እነዚህ ቀናት ካለፉ በኋላ፣ ንጉሡ በሱሳ ግንብ ለነበሩት፣ ከትንሽ እስከ ትልቅ ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ዙሪያውን በአትክልት በተከበበው አደባባይ ሰባት ቀን የፈጀ ግብዣ አደረገ።

6. አደባባዩም ከነጭና ከሰማያዊ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤ እነርሱም የብር ቀለበት በተበጀላቸው፣ ከነጭ በፍታና ከሐምራዊ ቀለም በተሠሩ ገመዶች በዕብነ በረዱ ምሰሶዎች ላይ ተንጠልጥለው ነበር። ነጭና ቀይ ቀለማት ተሰበጣጥረው በተነጠፉበት ወለል ላይ የወርቅና የብር ድንክ ዐልጋዎች ነበሩ፤ እነርሱም ከዕብነ በረድ፣ ቀስተ ደመና ከሚመስሉ ቀለሞችና ከሌሎች የከበሩ ድንጋዮች የተሠሩ ነበሩ።

7. የወይን ጠጁም አንዱ ከሌላው ልዩ በሆነ የወርቅ ዋንጫ ይቀርብ ነበር፤ ከንጉሡም ልግስና የተነሣ የቤተ መንግሥቱ የወይን ጠጅ የተትረፈረፈ ነበር።

8. ንጉሡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚፈልገውን ያህል እንዲያቀርቡለት የወይን ጠጅ አሳላፊዎቹን ሁሉ አዝዞ ስለ ነበረ፣ በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ ተስተናጋጅ እንዲጠጣ ተፈቅዶለት ነበር።

9. ንግሥት አስጢንም በንጉሥ ጠረክሲስ ቤተ መንግሥት እንደዚሁ ለሴቶች ግብዣ አድርጋ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 1