ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 7:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ከዚያም በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንድትተወው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ! አልሁ።

6. እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ጌታ እግዚአብሔር፣ “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለ።

7. ይህንም ደግሞ አሳየኝ፤ ጌታ በእጁ ቱምቢ ይዞ በቱምቢ በተሠራ ቅጥር አጠገብ ቆሞ ነበር።

8. እግዚአብሔር፣ “አሞጽ፣ የምታየው ምንድ ነው?” አለኝ።እኔም፣ “ቱምቢ” አልሁ።ጌታም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱምቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ አልምራቸውም።

9. “የይስሐቅ ማምለኪያ ኮረብታዎች ባድማ ይሆናሉ፤የእስራኤል መቅደሶች ይፈርሳሉ፤በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፌ እነሣለሁ።”

10. ከዚህ በኋላ የቤቴል ካህን አሜስያስ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዮርብዓም እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “አሞጽ በእስራኤል ቤት መካከል በአንተ ላይ እያሤረ ነው፤ ምድሪቱም ቃሉን ሁሉ ልትሸከም አትችልም፤

11. አሞጽ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበርና፤“ ‘ኢዮርብዓም በሰይፍ ይሞታል፤እስራኤልም በእርግጥ ከትውልድ አገሩተማርኮ ይሄዳል።”

12. አሜስያስም፣ አሞጽን እንዲህ አለው፤ “አንተ ባለ ራእይ ከዚህ ሂድ! ከይሁዳ ምድር ሽሽ፤ እዚያም እንጀራህን ብላ፤ በዚያም ትንቢት ተናገር።

13. ከእንግዲህ ወዲያ ግን በቤቴል ትንቢት አትናገር፤ የንጉሡ መቅደስ፣ የመንግሥቱም መኖሪያ ነውና።”

14. አሞጽም ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ እረኛና የባሉጥ ፍሬ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤

15. እግዚአብሔር ግን የበግ መንጋ ከምጠብቅበት ቦታ ወስዶ፣ ‘ሂድና ለሕዝቤ ለእስራኤል ትንቢት ተናገር’ አለኝ፤

16. እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ።አንተ፣ “ ‘በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፤በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ’ ትላለህ።

17. “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤”‘ሚስትህ በከተማዪቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፤ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፤ምድርህም እየተለካ ይከፋፈላል፤አንተ ራስህ በረከሰ ምድር ትሞታለህ፤እስራኤልም ከትውልድ አገሩ፣ተማርኮ ይሄዳል።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አሞጽ 7