ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የሞዓብ ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤የኤዶምን ንጉሥ ዐጥንት፣ዐመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎአልና፤

2. የቂርዮትን ምሽጎች እንዲበላ፣በሞዓብ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ሞዓብ በጦርነት ጩኸትና በመለከት ድምፅ መሐል፣በታላቅ ሁካታ ውስጥ ይሞታል።

3. ገዧን እደመስሳለሁ፣አለቆቿንም ሁሉ ከንጉሥዋ ጋር እገድላለሁ፤”ይላል እግዚአብሔር።

4. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የይሁዳ ኀጢአት፣ይልቁን ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋል፤ትእዛዙንም አልጠበቁምና፤አባቶቻቸው በተከተሏቸው አማልክት፣በሐሰት አማልክት በመመራት ስተዋልና።

5. የኢየሩሳሌምን ምሽጎች እንዲበላ፣በይሁዳ ላይ እሳት እሰዳለሁ።

በእስራኤል ላይ የተሰጠ ፍርድ

6. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የእስራኤል ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ጻድቁን ስለ ጥሬ ብር፣ችግረኛውንም ስለ ጥንድ ጫማ ይሸጡታልና።

7. የድኾችን ራስ፣ በምድር ትቢያ ላይይረግጣሉ፤ፍትሕንም ከጭቊኖች ይነጥቃሉ፤አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋር ይተኛሉ፤እንዲህም እያደረጉ ቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ።

8. በመያዣነት በተወሰደው ልብስ ላይ፣በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤በአምላካቸው ቤት፣በመቀጫነት የተወሰደውን የወይን ጠጅ ይጠጣሉ።

9. ቁመቱ እንደ ዝግባ፣ጥንካሬውም እንደ ባሉጥ ዛፍ የነበረ ቢሆንም፣አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁት፣ከላይ ፍሬውን፣ከታችም ሥሩን አጠፋሁ።

10. “የአሞራውያንን ምድር ልሰጣችሁ፣ከግብፅ አወጣኋችሁ፤አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መራኋችሁ።

11. ደግሞም ነቢያትን ከወንዶች ልጆቻችሁ መካከል፣ናዝራውያንንም ከጐልማሶቻችሁ መካከል አስነሣሁ፤የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ ይህ እውነት አይደለምን?”ይላል እግዚአብሔር።

12. “እናንተ ግን ናዝራውያኑን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ነቢያቱንም ትንቢት እንዳይናገሩ አዘዛችኋቸው።

13. “እነሆ፤ በእህል የተሞላ ጋሪ እንደሚያደቅ፣እኔም አደቃችኋለሁ።

14. ፈጣኑ አያመልጥም፤ብርቱውንም ብርታቱ አይረዳውም፤ኀያሉም ነፍሱን አያድንም።

15. ቀስተኛው በቦታው ጸንቶ አይቆምም፤ፈጣኑም ተዋጊ ሮጦ አያመልጥም፤ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም።

16. ጐበዞቹ ተዋጊዎች እንኳ፣በዚያ ቀን ዕራቁታቸውን ይሸሻሉ፤”ይላል እግዚአብሔር።