ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አሞጽ 1 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በቴቁሔ ከነበሩት እረኞች መካከል አንዱ የሆነው አሞጽ፣ ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንዲሁም የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ በነበረ ጊዜ፣ ይኸውም የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየውና የተናገረው ቃል ይህ ነው፤

2. እርሱም እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔር ከጽዮን ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማል፤ከኢየሩሳሌምም ያንጐደጒዳል፤የእረኞች ማሰማሪያዎች ደርቀዋል፤የቀርሜሎስም ዐናት ጠውልጎአል።”

በእስራኤል ጐረቤቶች ላይ የተሰጠ ፍርድ

3. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የደማስቆ ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤የብረት ጥርስ ባለው ማሄጃ፣ ገለዓድንአሂዳለችና፤

4. የወልደ አዴርን ምሽጎች እንዲበላ፣ በአዛሄልቤት ላይ እሳት እሰዳለሁ።

5. የደማስቆን በሮች እሰባብራለሁ፤በቤት ዔደን በትር የያዘውን፣በአዌን ሸለቆ ያለውን ንጉሥ እደመስሳለሁ፤የሶርያም ሕዝብ ተማርኮ ወደ ቂር ይሄዳል”ይላል እግዚአብሔር።

6. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የጋዛ ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ሕዝቡን ሁሉ ማርካ በመውሰድ፣ለኤዶም ሸጣለችና።

7. ምሽጎቿን እንዲበላ፣በጋዛ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰዳለሁ።

8. በአስቀሎና በትር የያዘውን፣የአሸዶድንም ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ በፍልስጥኤም ካሉት የመጨረሻው ሰውእስኪሞት ድረስ፣እጄን በአቃሮን ላይ እዘረጋለሁ፤”ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

9. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የጢሮስ ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም።የወንድማማችነትን ቃል ኪዳን በማፍረስ፣ሕዝቡን ሁሉ ማርካ ለኤዶም ሸጣለችና።

10. ምሽጎችዋን እንዲበላ፣በጢሮስ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰዳለሁ።”

11. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የኤዶም ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ርኅራኄን በመንፈግ፣ወንድሙን በሰይፍ አሳዶታልና፤የቊጣውንም ነበልባል ሳይገድብ፣መዓቱን ሳያቋርጥ አውርዶበታልና፤

12. የባሶራን ምሽጎች እንዲበላ፣በቴማን ቅጥሮች ላይ እሳት እሰዳለሁ።”

13. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ስለ ሦስቱ የአሞን ኀጢአት፣ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቊጣዬን አልመልስም፤ድንበሩን ለማስፋት፣የገለዓድን ነፍሰ ጡር ሴቶች ሆድ ቀዶአልና።

14. በጦርነት ቀን በጩኸት ውስጥ፣በማዕበል ቀን በዐውሎ ነፋስ ውስጥ፣ምሽጎቿን እንዲበላ፣በረባት ቅጥሮች ላይ እሳት እሰዳለሁ።

15. ንጉሥዋ ከሹማምንቱ ጋር፣በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፣”ይላል እግዚአብሔር።