ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ናሆም 3:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ለደም ከተማ ወዮላት!ሐሰት፣ዘረፋም ሞልቶባታል፤ብዝበዛዋ ተግዞ አያልቅም።

2. የጅራፍ ድምፅ፣የመንኰራኵር ኳኳቴ፣የፈጣን ፈረስ ኮቴ፣የሠረገሎች ድምፅ ተሰምቶአል

3. ፈረሰኛው ይጋልባል፤ሰይፍ ይንቦገቦጋል፤ጦር ያብረቀርቃል፤የሞተው ብዙ ነው፤ሬሳ በሬሳ ሆኖአል፤ስፍር ቍጥር የለውም፤መተላለፊያ አልተገኘም።

4. ይህ ሁሉ የሆነው ቅጥ ባጣች፣አሳሳችና መተተኛ በሆነች ዘማዊት ምክንያት ነው፤እርሷም በዝሙቷ አሕዛብን፣በጥንቈላዋም ሕዝቦችን ባሪያ ያደረገች ናት።

5. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“እኔ በጠላትነት ተነሥቼብሻለሁ፤ቀሚስሽን እስከ ፊትሽ እገልበዋለሁ፤ዕርቃንሽን ለአሕዛብ፣ኀፍረትሽንም ለነገሥታት አሳያለሁ።

6. ቍሻሻ እደፋብሻለሁ፤እንቅሻለሁ፤ማላገጫም አደርግሻለሁ።

7. የሚያዩሽ ሁሉ ከአንቺ እየሸሹ፣‘ነነዌ ፈራርሳለች፤ ማን ያለቅስላታል?’ ይላሉ፤የሚያጽናናሽንስ ከወዴት አገኛለሁ?”

8. አንቺ በዐባይ ወንዝ አጠገብ ካለችው፣በውሃ ከተከበበችው፣ከኖእ አሞን ትበልጫለሽን?ወንዙ መከላከያዋ፣ውሃውም ቅጥሯ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ናሆም 3