ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ናሆም 2:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ነነዌ ሆይ፤ አጥቂ መጥቶብሻል፤ምሽግሽን ጠብቂ፤መንገድሽን ሰልዪ፤ወገብሽን ታጠቂ፤ኀይልሽን ሁሉ አሰባስቢ።

2. አጥፊዎች ባድማ ቢያደርጓቸውም፣የወይን ተክል ቦታቸውን ቢያጠፉባቸውም፣እንደ እስራኤል ክብር ሁሉ፣ እግዚአብሔር የያዕቆብንም ክብር ይመልሳል።

3. የወታደሮቹ ጋሻ ቀይ ነው፤ተዋጊዎቹ ቀይ ልብስ ለብሰዋል፤ዝግጁ በሆኑበት ቀን፣የሠረገሎቹ ብረት ያብረቀርቃል፤የጦሩ ዘንግ ይወዛወዛል።

4. ሠረገሎች በአደባባይ ወዲያ ወዲህ ይከንፋሉ፤በመንገዶችም ላይ ይርመሰመሳሉ፤የሚንበለበል ፋና ይመስላሉ፤እንደ መብረቅም ይወረወራሉ።

5. ምርጥ ተዋጊዎቹን ይጠራል፤ዳሩ ግን መንገድ ላይ ይሰናከላሉ፤ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ይሮጣሉ፤መከላከያ ጋሻውም በቦታው አለ።

6. የወንዙ በር ወለል ብሎ ተከፈተ፤ቤተ መንግሥቱም ወደቀ።

7. ከተማዪቱ መማረኳና መወሰዷ እንደማይቀር፣አስቀድሞ ተነግሮአል፤ሴቶች ባሪያዎቿ እንደ ርግብ ያለቅሳሉ፤ደረታቸውንም ይደቃሉ።

8. ነነዌ እንደ ኵሬ ናት፤ውሃዋም ይደርቃል፤“ቁም! ቁም!” ብለው ይጮኻሉ፤ነገር ግን ወደ ኋላ የሚመለስ የለም።

9. ብሩን ዝረፉ፤ወርቁን ንጠቍ፤በየግምጃ ቤቱ ያለው፤የተከማቸውም ሀብት ስፍር ቍጥር የለውም።

10. ተበዝብዛለች፤ ተዘርፋለች፤ ተራቍታለች።ልብ ቀልጦአል፤ ጒልበት ተብረክርኮአል፤ሰውነት ተንቀጥቅጦአል፤ ፊት ሁሉ ገርጥቶአል።

11. አሁን ታዲያ የአንበሶቹ ዋሻ፣ደቦሎቻቸውን ያበሉበትወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፣ግልገሎችም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ቦታ ወዴት ነው?

12. አንበሳው ለግልገሎቹ የሚበቃውን ያህል ገደለ፤ለእንስቶቹም ዐንቆ ገደለላቸው፤የገደለውን በማረፊያ ቦታው፣የነጠቀውንም በዋሻው ሞልቶታል።

13. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በእናንተ ላይ ተነሥቼባችኋለሁ፤ሠረገሎቻችሁን አቃጥዬ አጨሳለሁ፤ደቦል አንበሶቻችሁን ሰይፍ ይበላል፤የምትበሉትን በምድር ላይ አልተውላችሁም፤የመልእክተኞቻችሁም ድምፅ፣ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ናሆም 2