ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ናሆም 1:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤

2. እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል

3. እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።

4. ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል።ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።

5. ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤ኰረብቶችም ቀለጡ።ምድር በፊቱ፣ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።

6. ቊጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል?ጽኑ ቊጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል?መዓቱ እንደ እሳት ፈሶአል፤ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።

7. እግዚአብሔር መልካም ነው፤በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው።ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤

8. ነነዌን ግን፣በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።

9. በእግዚአብሔር ላይ ምንም ቢያሤሩ፣እርሱ ያጠፋዋል፤መከራም ዳግመኛ አይነሣም።

10. በእሾህ ይጠላለፋሉ፤በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤እሳትም እንደ ገለባ ይበላቸዋል።

11. ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣ክፋትንም የሚመክር፣ከአንቺ ዘንድ ወጥቶአል።

12. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም።ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣ከእንግዲህ አላስጨንቅህም።

13. አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።”

14. አንቺ ነነዌ፤ እግዚአብሔር ስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዞአል፤“ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤በአማልክቶቻችሁ ቤት ያሉትን፣የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤አንተ ክፉ ነህና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ናሆም 1