ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 9:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “አብራምን የመረጥኸውና ከከለዳው ያንዑር አውጥተህ አብርሃም የሚል ስም የሰጠኸው አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ።

8. ልቡ ለአንተ የታመነ ሆኖ ስላገኘኸውም፣ የከነዓናውያንን የኬጢያውያንን፣ የአሞራውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የኢያቡሳውያንንና የጌርጌሳውያንን ምድር ለዘሮቹ ለመስጠት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባህ፤ ጻድቅ ስለ ሆንህም የሰጠኸውን ተስፋ ጠበቅህ።

9. “አንተ በግብፅ የአባቶቻችንን ሥቃይ አየህ፤ በቀይ ባሕርም ጩኸታቸውን ሰማህ።

10. ታምራታዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በፈርዖንና፣ በሹማምቱ ሁሉ፣ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ላክህ፤ ይህንም ያደረግኸው ግብፃውያን እንዴት በእብሪት እንዳስጨነቋቸው ስላወቅህ ነው። እስከ ዛሬም የሚጠራ ስም ለራስህ እንዲኖርህ አደረግህ።

11. በደረቅ ምድር እንዲሻገሩ ባሕሩን በፊታቸው ከፈልህ፤ ያሳደዷቸውን ግን በኀይለኛ ውሃ ውስጥ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ውስጥ ወረወርሃቸው።

12. ቀን በደመና ዐምድ፣ በሚሄዱበት መንገድ ታበራላቸውም ዘንድ ሌሊት በእሳት ዐምድ መራሃቸው።

13. “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው።

14. የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው።

15. በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው።

16. “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕ ተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም።

17. ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤

18. የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 9