ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 9:15-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው።

16. “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕ ተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም።

17. ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤

18. የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

19. “ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም።

20. ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው።

21. በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።

22. “በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ።

23. ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 9