ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 9:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዚያኑ ወር ሃያ አራተኛ ቀን እስራኤላውያን ጾመው፣ ማቅ ለብሰው፣ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው በአንድነት ተሰበሰቡ።

2. የእስራኤላውያን ዘር የሆኑትም ራሳቸውን ከባዕዳን ሁሉ ለዩ። ቆመውም ኀጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን በደል ተናዘዙ።

3. በያሉበትም ቦታ ቆመው ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሩብ ቀን አነበቡ፤ የቀረውን ሩብ ቀን ደግሞ ንስሓ በመግባትና ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር በመስገድ አሳለፉ።

4. ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ቀድምኤል፣ ሰበንያ፣ ቡኒ፣ ሰራብያ፣ ባኒ፣ ከናኒ፣ በመውጫ ደረጃዎች ላይ ቆሙ፤ ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅ ጮኹ።

5. ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ።“ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል።

6. አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ። ሰማያትን፣ ከሰማያት በላይ ያሉትን ሰማያትና የከዋክብታቸውን ሰራዊት ሁሉ፣ ምድርንና በላይዋ ያለውን ሁሉ፣ ባሕሮችንና በውስጣቸው ያሉትንም ሁሉ ፈጥረሃል። ለሁሉም ሕይወትን ትሰጣለህ፤ የሰማይ ሰራዊትም ይሰግዱልሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 9