ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 6:5-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ከዚያም ሰንባላጥ ለአምስተኛ ጊዜ ያንኑ መልእክት በረዳቱ ላከብኝ፤ በእጁም ማኅተም የሌለው ያልታሸገ ደብዳቤ ይዞ ነበር፤

6. የተጻፈበትም እንዲህ የሚል ነበር፤“አንተና አይሁዳውያን ለማመፅ እንደ ምትዶልቱና ቅጥሩንም እንደምትሠሩ በሕዝቦች መካከል ተወርቶአል፤ ጌሳምም እውነት መሆኑን አረጋግጦአል፤ ከዚህም በተጨማሪ በተወራው መሠረት አንተ ንጉሣቸው እንደምትሆን፣

7. ስለ አንተም ‘በአይሁድ ንጉሥ አለ’ ብለው በኢየሩሳሌም የሚያውጁ ነቢያትን እንኳ ሳይቀር እንደ ሾምህ ተወርቷል፤ ይህም ነገር ለንጉሡ መድረሱ አይቀርም፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”

8. እኔም “አንተ የምትለውን የመሰለ ምንም ነገር አልተደረገም፤ ይህ አንተ በአእምሮህ የፈጠርኸው ነው” ብዬ መልስ ላክሁበት።

9. ሁሉም፣ “እጃቸው መሥራት እስኪሳነው ድረስ ይዝላል፤ ሥራውም ሳይጠናቀቅ ይቀራል” ብለው በማሰብ ሊያስፈራሩን ሞከሩ። እኔ ግን፣ “አሁንም እጄን አበርታ” ስል ጸለይሁ።

10. አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።

11. እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ።

12. በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦብያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ።

13. በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።

14. አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦብያንና ሰንባላጥን አስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም አስብ።

15. ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ።

16. ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን ሲሰሙ፣ በዙሪያችን ያሉ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ በራሳቸው መተማመንም አልቻሉም፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን ርዳታ መሆኑን ተገንዝበዋል።

17. በዚያን ጊዜ የይሁዳ መኳንንት ለጦብያ ብዙ ደብዳቤ ይልኩ ነበር፤ ከጦብያም መልስ ይላክላቸው ነበር።

18. በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎች ምለውለት ነበር፤ ምክንያቱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማት ከመሆኑም በላይ ልጁ የሆሐናን የሌራክያን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 6