ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 6:10-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አንድ ቀን ቤቱ በላዩ ላይ ተዘግቶበት ወደ ነበረው ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ሄድሁ፤ እርሱም፣ “ሰዎች ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በርግጥም በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር ቤት ባለው በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፤ የቤተ መቅደሱንም በሮች እንዝጋቸው” አለኝ።

11. እኔ ግን፣ “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ ይደበቃል? ወይም ደግሞ ሕይወቱን ለማዳን ሲል ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ይገባዋልን? አልሄድም!” አልሁ።

12. በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦብያና ሰንባላጥ በገንዘብ ስለ ደለሉት እንጂ እግዚአብሔር ወደ እኔ እንዳልላከው ተረዳሁ።

13. በገንዘብ የተገዛው እኔን ለማስፈራራት ነው፤ ይኸውም ይህን በመፈጸም ኀጢአት እንድሠራና በዚህም መጥፎ ስም ሰጥተው ተቀባይነት እንዳይኖረኝ ለማድረግ ነው።

14. አምላኬ ሆይ፤ ስለ ፈጸሙት ድርጊት ጦብያንና ሰንባላጥን አስብ፤ ሊያስፈራሩኝ የሞከሩትን ነቢያቱን ኖዓድያንና ሌሎቹን ነቢያትም አስብ።

15. ቅጥሩም ኤሉል በተባለው ወር ሃያ አምስተኛ ቀን፣ በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ።

16. ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን ሲሰሙ፣ በዙሪያችን ያሉ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፤ በራሳቸው መተማመንም አልቻሉም፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ የተከናወነው በአምላካችን ርዳታ መሆኑን ተገንዝበዋል።

17. በዚያን ጊዜ የይሁዳ መኳንንት ለጦብያ ብዙ ደብዳቤ ይልኩ ነበር፤ ከጦብያም መልስ ይላክላቸው ነበር።

18. በይሁዳ የሚኖሩ ሰዎች ምለውለት ነበር፤ ምክንያቱም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማት ከመሆኑም በላይ ልጁ የሆሐናን የሌራክያን ሴት ልጅ አግብቶ ነበር።

19. ከዚህም በተጨማሪ ስለ መልካም ሥራው በየጊዜው ይነግሩኝና እኔም ያልሁትን ይነግሩት ነበር፤ ጦብያም እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤ ይልክብኝ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 6