ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 2:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ከዚያም ንጉሡ አጠገቡ ከተቀመጠችው ንግሥት ጋር በመሆን፣ “ጒዞህ ምን ያህል ቀን ይፈጃል? መቼስ ትመለሳለህ?” ሲል ጠየቀኝ። ንጉሡም እኔን ለመስደድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ወሰንሁ።

7. ደግሞም እንዲህ አልሁት፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በደኅና እንዲያሳልፉኝ ከኤፍራጥስ ማዶ ላሉት አገረ ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤

8. እንዲሁም ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ፣ በቤተ መቅደሱ አጠገብ ላለው ግምብ በሮች፣ ለከተማዪቱ ቅጥርና እኔም ለምገባበት ቤት ሠረገላ የሚሆን እንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤” መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ነበረችና ንጉሡም ፈቀደልኝ።

9. ስለዚህ በኤፍራጥስ ማዶ ወደሚገኙት አገረ ገዦች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው፤ ንጉሡም የጦር አለቆችና ፈረሰኞች አብረውኝ እንዲሄዱ አድርጎ ነበር።

10. ሖሮናዊው ሰንባላጥና አሞናዊው ሹም ጦብያ ይህን በሰሙ ጊዜ ስለ እስራኤላውያን ደኅንነት የሚቈረቈር ሰው በመምጣቱ እጅግ ተበሳጩ።

11. እኔም ወደ ኢየሩሳሌም ሄድሁ፤ በዚያም ሦስት ቀን ከቈየሁ በኋላ፣

12. ከጥቂት ሰዎች ጋር በሌሊት ወጣሁ። ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ እግዚአብሔር በልቤ ያኖረውን ነገር ለማንም አልነገርሁም፤ ከተቀመጥሁበት እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ሌሎች እንስሳት አልነበሩም።

13. በሌሊትም ወጥቼ በሸለቆው በር በኩል አድርጌ ወደ ዘንዶው የውሃ ጒድጓድና ወደ ቆሻሻ መድፊያው በር ሄድሁ፤ የፈረሱትንም የኢየሩሳሌምን ቅጥሮችና በእሳት የወደሙትን በሮች ተመለከትሁ።

14. ከዚያም ወደ ውሃ ምንጭ በርና ወደ ንጉሡ ኵሬ ሄድሁ፤ ይሁን እንጂ የተቀመጥሁበትን እንስሳ ማሳለፍ የሚያስችል በቂ ቦታ አልነበረም።

15. ስለዚህ ቅጥሩን እየተመለከትሁ ሌሊቱን ሸለቆውን ዐልፌ ወደ ላይ ወጣሁ፤ በመጨረሻም ተመልሼ በሸለቆው በር በኩል ገባሁ።

16. ለአይሁድ ወይም ለካህናቱ ወይም ለመኳንንቱ ወይም ለሹማምቱ ወይም ሥራውን ለሚሠሩት ሰዎች ገና ምንም የተናገርሁት ነገር ስላልነበረ፣ ወዴት እንደሄድሁ ወይም ምን እንዳደረግሁ ሹማምቱ አላወቁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 2