ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 10:30-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. “ሴት ልጆቻችንን በዙሪያችን ላሉት አሕዛብ አንሰጥም፤ የእነርሱን ሴቶች ልጆች ለወንዶች ልጆቻችን አንወስድም።

31. “አሕዛብ ጎረቤቶቻችን በሰንበት ቀን ለመሸጥ ሸቀጣ ሸቀጥ ወይም እህል ቢያመጡ፣ በሰንበት ወይም በማናቸውም በተቀደሰ ቀን ከእነርሱ አንገዛም። በየሰባት ዓመቱም ምድሪቱን እናሳርፋለን፤ ዕዳንም ሁሉ እንሠርዛለን።

32. “በየዓመቱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት የሚሆን የሰቅል አንድ ሦስተኛ ለመስጠት ቃል እንገባለን፤

33. ይህም በጠረጴዛው ላይ ለሚቀርበው ገጸ ኅብስት፣ ዘወትር ለሚቀርበው የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ በሰንበት፣ በወር መባቻና በተደነገጉ በዓላት ለሚቀርበው መሥዋዕት፣ ለተቀደሱ መባዎች፣ ለእስራኤል ስርየት ለሚቀርበው የኀጢአት መሥዋዕትና ለአምላካችን ቤት ሥራ ሁሉ የሚውል ነው።

34. “እኛ፣ ማለት ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና ሕዝቡ በየዓመቱ በተወሰነው ጊዜ በሕጉ እንደ ተጻፈው፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚነደውን ዕንጨት የእያንዳንዳችን ቤተ ሰብ መቼ ወደ አምላካችን ቤት ማምጣት እንዳለበት ለመወሰን ዕጣ ተጣጣልን።

35. “የሰብላችንንና የእያንዳንዱን ዛፍ ፍሬ በኵራትም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለማምጣት ቃል እንገባለን።

36. “እንዲሁም በሕጉ እንደ ተጻፈው የወንድ ልጆቻችንንና፣ የቀንድ ከብቶቻችንን፣ የመንጋዎቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን በኵራት ወደ አምላካችን ቤት፣ ወደሚያገለግሉትም ካህናት እናመጣለን።

37. “ከዚህም በላይ የቡሆአችንን፣ የእህል ቍርባናችንን፣ የዛፎቻችንን ፍሬ ሁሉ፣ አዲሱን የወይን ጠጃችንንና የዘይታችንን በኵራት ወደ ካህናቱ፣ ወደ አምላካችን ቤት ዕቃ ቤቶች እናመጣለን። እኛ በምንሠራባቸው ከተሞች ሁሉ ያለውን ዐሥራት የሚሰበስቡት ሌዋውያን ስለሆኑ፣ የሰብላችንን ዐሥራት ወደ ሌዋውያኑ እናመጣለን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 10