ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሰቆቃወ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኛ ላይ የደረሰውን አስብ፤ውርደታችንን እይ፤ ተመልከትም።

2. ርስታችን ለመጻተኞች፣ቤቶቻችን ለባዕዳን ዐልፈው ተሰጡ።

3. ወላጅ አልባና አባት የሌላቸው ሆንን፤እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ።

4. ለምንጠጣው ውሃ መክፈል ነበረብን፤ዕንጨታችንንም የምናገኘው በግዢ ነበር።

5. የሚያሳድዱን ከተረከዞቻችን ሥር ናቸው፤ተጨንቀናል ዕረፍትም አጥተናል።

6. እንጀራ እንጠግብ ዘንድ፣ለአሦርና ለግብፅ እጃችንን ሰጠን።

7. አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው አለፉ፤እኛም የእነርሱን ቅጣት ተሸከምን።

8. ባሮች ሠልጥነውብናል፤ከእጃቸው ነጻ የሚያወጣን ማንም የለም።

9. በምድረ በዳ ካለው ሰይፍ የተነሣ፣በሕይወታችን ተወራርደን እንጀራ አገኘን።

10. ቈዳችን እንደ ምድጃ ጠቍሮአል፤በራብም ተቃጥሎአል።

11. ሴቶች በጽዮን፣ደናግል በይሁዳ ከተሞች ተደፈሩ።

12. መሳፍንት በእነርሱ እጅ ተሰቀሉ፤ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።

13. ጐልማሶች ወፍጮ እንዲፈጩ ተገደዱ፤ወንዶች ልጆች በዕንጨት ሸክም ተንገዳገዱ።

14. ሽማግሌዎች ከከተማዪቱ በር ሄደዋል፤ጐልማሶች ዝማሬያቸውን አቁመዋል።

15. ደስታ ከልባችን ጠፍቶአል፤ጭፈራችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል።

16. አክሊላችን ከራሳችን ላይ ወድቆአል፤ወዮልን፤ ኀጢአት ሠርተናልና!

17. ከዚህ የተነሣ ልባችን ደከመ፤ከእነዚህ የተነሣም ዐይናችን ፈዘዘ፤

18. ባዶዋን የቀረችው የጽዮን ተራራ፣የቀበሮዎች መፈንጫ ሆናለችና።

19. አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ለዘላለም ትገዛለህ፤ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።

20. ስለ ምን ፈጽመህ ትረሳናለህ?ስለምንስ ለረዥም ጊዜ ትተወናለህ?

21. እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም እንመለሳለን፤ዘመናችንን እንደ ቀድሞው አድስ፤

22. ፈጽመህ ካልጣልኸን፣ከመጠን በላይ ካልተቈጣኸን።