ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሰቆቃወ 4:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኖአል፤በውስጧ፣የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና።

14. እንደ ታወሩ ሰዎች፣በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣በደም እጅግ ረክሰዋል።

15. ሰዎች “ሂዱ! እናንት ርኵሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤“ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣“ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ።

16. እግዚአብሔር ራሱ በትኖአቸዋል፤ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤ካህናቱ አልተከበሩም፤ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም።

17. ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣ዐይኖቻችን ደከሙ፤ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን።

18. ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤መጨረሻችን ቀርቦአል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤ፍጻሜያችን መጥቶአልና።

19. ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤በተራሮች ላይ አሳደዱን፤በምድረ በዳም ሸመቁብን።

20. በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣በወጥመዳቸው ተያዘ፤በጥላው ሥር፣በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሰቆቃወ 4