ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሰቆቃወ 1:11-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እንጀራ በመፈለግ፣ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤በሕይወት ለመኖር፣የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤እኔ ተዋርጃለሁና።”

12. “እናንት መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን?ተመልከቱ፤ እዩም፤በጽኑ ቍጣው ቀን፣ እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣በእኔ ላይ የደረሰውን፣የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?

13. “ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤ወደ ኋላም ጣለኝ፤ቀኑን ሙሉ በማድከም፣ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ።

14. “ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤ኀይሌንም አዳከመ፤ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ።

15. “በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ፣እግዚአብሔር ተቃወመ፤ጒልማሶቼን ለማድቀቅ፣ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ፤ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።

16. “የማለቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ነው፤ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፣ሊያጽናናኝ የቀረበ፣መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም፤ጠላት በርትቶአልናልጆቼ ተጨንቀዋል።”

17. ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤የሚያጽናናትም የለም፤ጎረቤቶቹ ጠላቶቹ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር በያዕቆብ ላይ ትእዛዝ አውጥቶአል፤ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው፣እንደ ርኵስ ነገር ተቈጠረች።

18. “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤መከራዬንም ተመልከቱ፤ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቶቼ፣ተማርከው ሄደዋል።

19. “ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤እነርሱ ግን ከዱኝ፤ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ፣ሕይወታቸውን ለማትረፍ፣ምግብ ሲፈልጉ፣በከተማዪቱ ውስጥ አለቁ።

20. “አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ተጨንቄአለሁ!በውስጤ ተሠቃይቼአለሁ፤በልቤ ታውኬአለሁ፤እጅግ ዐመፀኛ ሆኛለሁና፤በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤በቤትም ውስጥ ሞት አለ።

21. “ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤አቤቱ የተናገርኻት ቀን ትምጣ፤እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሰቆቃወ 1