ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 8:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. አንደበቴ እውነትን ይናገራል፤ከንፈሮቼ ክፋትን ይጸየፋሉና።

8. ከአንደበቴ የሚወጡት ቃሎች ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤አንዳቸውም ጠማማና ግራ የሚያጋቡ አይደሉም።

9. በጥልቅ ለሚያስተውሉ ሁሉም ቀና ናቸው፤ዕውቀት ላላቸውም ስሕተት የለባቸውም።

10. ከብር ይልቅ ምክሬን፣ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤

11. ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናትና፤ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።

12. “እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋር አብሬ እኖራለሁ፤ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።

13. እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።

14. ምክርና ትክክለኛ ፍርድ የእኔ ናቸው፤ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።

15. ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤

16. መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ።

17. የሚወዱኝን እወዳቸዋለሁ፤ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።

18. ሀብትና ክብር፣ዘላቂ ብልጽግናና ስኬት በእኔ ዘንድ አሉ።

19. ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤ስጦታዬም ከነጠረ ብር።

20. እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፤በፍትሕም ጐዳና እጓዛለሁ፤

21. ለሚወዱኝ ብልጽግና እሰጣለሁ፤ግምጃ ቤታቸውንም እሞላለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 8