ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 8:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋር አብሬ እኖራለሁ፤ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።

13. እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።

14. ምክርና ትክክለኛ ፍርድ የእኔ ናቸው፤ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።

15. ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤

16. መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ።

17. የሚወዱኝን እወዳቸዋለሁ፤ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።

18. ሀብትና ክብር፣ዘላቂ ብልጽግናና ስኬት በእኔ ዘንድ አሉ።

19. ፍሬዬ ከንጹሕ ወርቅ ይበልጣል፤ስጦታዬም ከነጠረ ብር።

20. እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፤በፍትሕም ጐዳና እጓዛለሁ፤

21. ለሚወዱኝ ብልጽግና እሰጣለሁ፤ግምጃ ቤታቸውንም እሞላለሁ።

22. እግዚአብሔር ከቀድሞ ሥራዎቹ በፊት፣የተግባሮቹ መጀመሪያ አድርጎ አመጣኝ፡

23. ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ፣ከጥንት ከዘላለም ተሾምሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 8