ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 8:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ጥበብ ጮኻ አትጣራምን?ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን?

2. በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤

3. ወደ ከተማዪቱ በሚያስገቡት በሮች አጠገብ፣በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤

4. “ሰዎች ሆይ፤ የምጠራውኮ እናንተን ነው፤ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፄን ከፍ አደርጋለሁ።

5. እናንተ ብስለት የጐደላችሁ፤ ጠንቃቃነትን ገንዘብ አድርጉ፤እናንተ ተላሎች፤ ማስተዋልን አትርፉ።

6. የምናገረው ጠቃሚ ነገር ስላለኝ አድምጡኝ፤ቀና ነገር ለመናገር ከንፈሮቼን እከፍታለሁ።

7. አንደበቴ እውነትን ይናገራል፤ከንፈሮቼ ክፋትን ይጸየፋሉና።

8. ከአንደበቴ የሚወጡት ቃሎች ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤አንዳቸውም ጠማማና ግራ የሚያጋቡ አይደሉም።

9. በጥልቅ ለሚያስተውሉ ሁሉም ቀና ናቸው፤ዕውቀት ላላቸውም ስሕተት የለባቸውም።

10. ከብር ይልቅ ምክሬን፣ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ፤

11. ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናትና፤ከምትመኙት ነገር ሁሉ አንዳች የሚስተካከላት የለም።

12. “እኔ ጥበብ ከማስተዋል ጋር አብሬ እኖራለሁ፤ዕውቀትና ልባምነት ገንዘቦቼ ናቸው።

13. እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን መጥላት ነው፤እኔም ትዕቢትንና እብሪትን፣ክፉ ጠባይንና ጠማማ ንግግርን እጠላለሁ።

14. ምክርና ትክክለኛ ፍርድ የእኔ ናቸው፤ማስተዋል አለኝ፤ ብርታት አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 8