ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 3:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው።

4. በዚያን ጊዜ ሞገስንና መልካም ስምን፣በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ።

5. በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤

6. በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።

7. በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።

8. ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል።

9. እግዚአብሔርን በሀብትህ፣ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤

10. ይህን ብታደርግ፣ ጎተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል።

11. ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤በዘለፋውም አትመረር፤

12. አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻልና።

13. ጥበብን የሚያገኛት፣ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤

14. እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና።

15. ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም።

16. በቀኝ እጇ ረጅም ዕድሜ አለ፤በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች።

17. መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው።

18. ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤የሚይዟትም ይባረካሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 3