ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 3:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤

22. ለነፍስህ ሕይወት፣ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ።

23. ከዚያም መንገድህን በሰላም ትሄዳለህ፤እግርህም አይሰናከልም፤

24. ስትተኛ አትፈራም፤ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።

25. ድንገተኛን መከራ፣በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤

26. እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል።

27. ማድረግ እየቻልህለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ።

28. አሁን በእጅህ እያለ፣ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።

29. አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት።

30. ምንም ጒዳት ሳያደርስብህ፣ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ።

31. በክፉ ሰው አትቅና፤የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤

32. እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል።

33. የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል።

34. እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል።

35. ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 3