ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 25:8-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣው፤ባልንጀራህ ካሳፈረህ፣ኋላ ምን ይውጥሃል?

9. ስለ ራስህ ጒዳይ ከባልንጀራህ ጋር በምትከራከርበት ጊዜ፣የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ፤

10. ያለዚያ ይህን የሚሰማ ያሳፍርሃል፤አንዴ የጠፋውን ስምህንም ፈጽሞ መመለስ አትችልም።

11. ባግባቡ የተነገረ ቃል፣በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።

12. የጠቢብ ሰው ዘለፋ ለሚሰማ ጆሮ፣እንደ ወርቅ ጒትቻ ወይም እንደ ጥሩ የወርቅ ጌጥ ነው።

13. በመከር ጊዜ የበረዶ ቅዝቃዜ ለሰስ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ታማኝ መልእክተኛም ለላኩት እንደዚሁ ነው፤የጌቶቹን መንፈስ ያሳርፋልና።

14. የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጒራ የሚነዛ ሰው፣ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።

15. በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል።

16. ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤ከበዛ ያስመልስሃል።

17. ወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ፤ታሰለቸውና ይጠላሃል።

18. በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሰክር፣እንደ ቈመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ተሳለ ፍላጻ ነው።

19. በመከራ ጊዜ በወስላታ ሰው መተማመን፣በተበላሸ ጥርስና በሰለለ እግር እንደ መታመን ነው።

20. ላዘነ ልብ የሚዘምር፣በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣ወይም በሶዳ ላይ እንደ ተጨመረ ሆምጣጤ ነው።

21. ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ቢጠማም ውሃ አጠጣው።

22. ይህን በማድረግህም፣ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህ፤ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይከፍልሃል።

23. የሰሜን ነፋስ ዝናብ እንደሚያመጣ ሁሉ፣ሐሜተኛ ምላስም ቊጡ ፊት ታስከትላለች።

24. ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር፣በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል።

25. ከሩቅ የሚመጣ መልካም ዜና፣የተጠማችን ነፍስ እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውሃ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 25