ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 25:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እነዚህ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዷቸው ሌሎች የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው፦

2. ነገርን መሰወር ለእግዚአብሔር ክብሩ ነው፤ነገርን ፈልፍሎ ማውጣት ግን ለነገሥታት ክብራቸው ነው።

3. ሰማያት ከፍ ያሉ እንደሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደሆነች ሁሉ፣የነገሥታትም ልብ እንደዚሁ አይመረመርም።

4. ከብር ዝገትን አስወግድ፤አንጥረኛውም ንጹሕ ነገር ያገኛል፤

5. ክፉን ከንጉሥ ፊት አርቅ፤ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።

6. በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤በታላላቆች መካከል መገኘትም አይመርህ፤

7. በትልቅ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ፣ራሱ፣ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና።በዐይንህ ያየኸውን ሁሉ፣

8. ወደ ፍርድ አደባባይ በችኰላ አታውጣው፤ባልንጀራህ ካሳፈረህ፣ኋላ ምን ይውጥሃል?

9. ስለ ራስህ ጒዳይ ከባልንጀራህ ጋር በምትከራከርበት ጊዜ፣የሌላውን ሰው ምስጢር አታውጣ፤

10. ያለዚያ ይህን የሚሰማ ያሳፍርሃል፤አንዴ የጠፋውን ስምህንም ፈጽሞ መመለስ አትችልም።

11. ባግባቡ የተነገረ ቃል፣በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።

12. የጠቢብ ሰው ዘለፋ ለሚሰማ ጆሮ፣እንደ ወርቅ ጒትቻ ወይም እንደ ጥሩ የወርቅ ጌጥ ነው።

13. በመከር ጊዜ የበረዶ ቅዝቃዜ ለሰስ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ታማኝ መልእክተኛም ለላኩት እንደዚሁ ነው፤የጌቶቹን መንፈስ ያሳርፋልና።

14. የማይለግሰውን ስጦታ እቸራለሁ ብሎ ጒራ የሚነዛ ሰው፣ዝናብ እንደሌለው ደመናና ነፋስ ነው።

15. በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል፤ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል።

16. ማር ስታገኝ በልክ ብላ፤ከበዛ ያስመልስሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 25