ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 23:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከገዥ ጋር ለመብላት በምትቀመጥበት ጊዜ፣በፊትህ ያለውን በሚገባ አስተውል፤

2. ስግብግብም ብትሆን እንኳ፣በጒሮሮህ ላይ ካራ አጋድምበት፤

3. የእርሱ ጣፋጭ መብል አያስጐምጅህ፤ምግቡ አታላይ ነውና።

4. ሀብት ለማግኘት ስትል ራስህን አታድክም፤ሐሳብህን የመግታት ጥበብ ይኑርህ።

5. በሀብት ላይ ዐይንህን ብትጥል፤ወዲያው ይጠፋል፤ወደ ሰማይ እንደሚበርር ንስር፣ በርግጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል፤

6. የስስታምን ምግብ አትብላ፤ጣፋጭ መብሉም አያስጐምጅህ፤

7. ሁል ጊዜ ስለ ዋጋ የሚያሰላ ሰው ነውና፤“ብላ፣ ጠጣ” ይልሃል፤ልቡ ግን ከአንተ ጋር አይደለም።

8. የበላሃት ትንሿ እንኳ ታስመልስሃለች፤የምስጋና ቃልህንም ከንቱ ታደርጋለህ።

9. ከጅል ጋር አትነጋገር፤የቃልህን ጥበብ ያንኳስሳልና።

10. የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ፤አባት የሌላቸውንም ልጆች መሬት አትግፋ፤

11. ታዳጊያቸው ብርቱ ነውና፤እርሱ ይፋረድላቸዋል።

12. ልብህን ለምክር፣ጆሮህንም ለዕውቀት ቃል ስጥ።

13. ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል፤በአርጩሜ ብትገርፈው አይሞትም።

14. በአርጩሜ ቅጣው፤ነፍሱንም ከሞት አድናት።

15. ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 23