ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 21:12-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ጻድቁ የክፉዎችን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ክፉዎችንም ያጠፋቸዋል።

13. ሰው የድኾችን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን ቢዘጋ፣እርሱም ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።

14. በስውር የተደረገ ስጦታ ቊጣን ያበርዳል፤በጒያ የተሸሸገ እጅ መንሻም ታላቅ ቊጣን ጸጥ ያደርጋል።

15. ፍትሕ ሲሰፍን ጻድቁን ደስ ያሰኘዋል፤ክፉ አድራጊዎችን ግን ያሸብራል።

16. የማስተዋልን መንገድ የሚስት ሰው፣በሙታን ጉባኤ ያርፋል።

17. ቅንጦትን የሚወድ ይደኸያል፤የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድም ባለጠጋ አይሆንም።

18. ክፉ ሰው ለጻድቅ፣ወስላታም ለቅን ሰው ወጆ ይሆናል።

19. ከጨቅጫቃና ከቊጡ ሚስት ጋር ከመኖር፣በምድረ በዳ መኖር ይሻላል።

20. በጠቢብ ቤት ምርጥ ምግብና ዘይት ተከማችቶ ይገኛል፤ተላላ ሰው ግን ያለ የሌለውን ያሟጥጣል።

21. ጽድቅንና ፍቅርን የሚከተል፤ሕይወትን ብልጽግናንና ክብርን ያገኛል።

22. ጠቢብ የኀያላንን ከተማ ቅጥር ጥሶ ይገባል፤መታመኛ ምሽጋቸውንም ያፈርሳል።

23. አንደበቱንና ምላሱን የሚቈጣጠር፣ራሱን ከመቅሠፍት ይጠብቃል።

24. ትዕቢተኛና ኵሩ ሰው፣ ኋፌዘኛቃ ይባላል፤በጠባዩም እብሪተኛ ነው።

25. ታካችን የሚገድለው ምኞቱ ነው፤እጆቹ መሥራት አይፈልጉምና።

26. ክፉ ሰው ቀኑን ሙሉ ይመኛል፤ጻድቅ ግን አንዳች ሳያስቀር ይሰጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 21