ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 20:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ብዙ ሰው ጽኑ ፍቅር እንዳለው ይናገራል፤ታማኝን ሰው ግን ማን ሊያገኘው ይችላል?

7. ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ከእርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ቡሩካን ናቸው።

8. ንጉሥ ለፍርድ ዙፋኑ ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ክፉውን ሁሉ በዐይኖቹ አበጥሮ ይለያል።

9. ለመሆኑ፣ “ልቤን በንጽሕና ጠብቄአለሁ፤ንጹሕ ነኝ፤ ኀጢአት የለብኝም” የሚል ማን ነው?

10. ሁለት ዐይነት ሚዛን፣ ሁለት ዐይነት መስፈሪያ፣ሁለቱንም እግዚአብሔር ይጸየፋቸዋል።

11. ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ከአድራጎቱ ይታወቃል።

12. የሚሰሙ ጆሮዎች፣ የሚያዩ ዐይኖች፣ሁለቱንም እግዚአብሔር ሠርቷቸዋል።

13. እንቅልፍ አትውደድ፤ አለዚያ ድኻ ትሆናለህ፤ዐይንህን ክፈት፤ የተትረፈረፈ ምግብ ይኖርሃል።

14. ዕቃ የሚገዛ፣ “የማይረባ ነው፤ የማይረባ ነው” ብሎ ያራክሳል፤ሲመለስ ግን በግዢው ይኵራራል።

15. ወርቁም አለ፤ ቀዩም ዕንቊ ተትረፍርፎአል፤ዕውቀት የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ብርቅ ጌጦች ናቸው።

16. ለማይታወቅ ሰው ዋስ የሆነውን ልብሱን ግፈፈው፤ለዘልዛላ ሴት የተዋሰውን በቃሉ ያዘው።

17. ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል።

18. ምክር ጠይቀህ ዕቅድ አውጣ፤ጦርነት የምትገጥም ከሆነ መመሪያ ተቀበል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 20