ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 2:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ማስተዋልም ይጠብቅሃል።

12. ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤

13. እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፣ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤

14. ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው፣በክፋት ጐዳና ሐሤት የሚያደርጉ፣

15. መንገዳቸው ጠማማ፣በአካሄዳቸው ጠመዝማዞች ናቸው።

16. ከአመንዝራ ሴትም ትጠብቅሃለች፤በአንደበቷም ከምታታልል ዘልዛላ ታድንሃለች፤

17. ይህችም የልጅነት ባሏን የተወች፣በአምላኳ ፊት የገባችውን ኪዳን ያቃለለች ናት።

18. ቤቷ ወደ ሞት ያደርሳል፤መንገዷም ወደ መናፍስተ ሙታን ያመራል።

19. ወደ እርሷ የሚገባ ማንም አይመለስም፤የሕይወትንም መንገድ አያገኝም።

20. አንተም በደጋግ ሰዎች ጐዳና ትሄዳለህ፤የጻድቃንንም መንገድ ይዘህ ትጓዛለህ።

21. ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ።

22. ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 2