ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 17:8-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እጅ መንሻ ለሰጭው እንደ ድግምት ዕቃ ነው፤በሄደበትም ቦታ ሁሉ ይሳካለታል።

9. በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል።

10. መቶ ግርፋት ተላላን ከሚሰማው ይልቅ፣ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል።

11. ክፉ ሰው ዐመፅን ብቻ ይፈልጋል፤በእርሱም ላይ ጨካኝ መልእክተኛ ይላክበታል።

12. ተላላን በቂልነቱ ከመገናኘት፣ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።

13. በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልስ ሰው፣ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም።

14. ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ።

15. በደለኛውን ንጹሕ ማድረግ ሆነ፣ ንጹሑን በደለኛ ማድረግ፣ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ናቸው።

16. ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣ተላላ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?

17. ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።

18. ማስተዋል የጐደለው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤ለወዳጁም ዋስ ይሆናል።

19. ጠብ የሚወድ ኀጢአትን ይወዳል፤በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል።

20. ጠማማ ልብ ያለው ሰው አይሳካለትም፤በአንደበቱ የሚቀላምድም መከራ ላይ ይወድቃል።

21. ተላላ ልጅ መውለድ ሐዘን ያስከትላል፤የተላላም አባት ደስታ የለውም።

22. ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል።

23. ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣በስውር ጒቦ ይቀበላል።

24. አስተዋይ ሰው ጥበብን ከፊቱ አይለያትም፤የተላሎች ዐይኖች ግን እስከ ምድር ዳርቻ ይንከራተታሉ።

25. ተላላ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል።

26. ንጹሑን ሰው መቅጣት ተገቢ አይደለም፤ሹሞችን ስለ ቅንነታቸው መግረፍ መልካም አይደለም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 17