ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 17:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እኵይ ሰው ክፉ ንግግር ያዳምጣል፤ሐሰተኛም የተንኰለኛን አንደበት በጥንቃቄ ይሰማል።

5. በድኾች የሚያፌዝ ፈጣሪያቸውን ይንቃል፤በሌላው ሰው መከራ ደስ የሚለው ከቅጣት አያመልጥም።

6. የልጅ ልጆች ለአረጋውያን ዘውድ ናቸው፤ወላጆችም ለልጆቻቸው አለኝታ ናቸው።

7. መልካም አነጋገር ለተላላ አይሰምርለትም፤ለገዥማ ሐሰተኛ አንደበት የቱን ያህል የከፋ ይሆል!

8. እጅ መንሻ ለሰጭው እንደ ድግምት ዕቃ ነው፤በሄደበትም ቦታ ሁሉ ይሳካለታል።

9. በደልን የሚሸፍን ፍቅርን ያዳብራል፤ነገርን የሚደጋግም ግን የልብ ወዳጆችን ይለያያል።

10. መቶ ግርፋት ተላላን ከሚሰማው ይልቅ፣ተግሣጽ ለአስተዋይ ጠልቆ ይሰማል።

11. ክፉ ሰው ዐመፅን ብቻ ይፈልጋል፤በእርሱም ላይ ጨካኝ መልእክተኛ ይላክበታል።

12. ተላላን በቂልነቱ ከመገናኘት፣ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።

13. በበጎ ፈንታ ክፉ የሚመልስ ሰው፣ክፉ ነገር ከቤቱ አይርቅም።

14. ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ።

15. በደለኛውን ንጹሕ ማድረግ ሆነ፣ ንጹሑን በደለኛ ማድረግ፣ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ናቸው።

16. ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣ተላላ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው?

17. ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።

18. ማስተዋል የጐደለው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤ለወዳጁም ዋስ ይሆናል።

19. ጠብ የሚወድ ኀጢአትን ይወዳል፤በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 17