ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 1:22-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. “እናንት ብስለት የሌላችሁ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወዱታላችሁ?ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?

23. ዘለፋዬን ብትሰሙኝ ኖሮ፣ልቤን ባፈሰስሁላችሁ፣ሐሳቤንም ባሳወቅኋችሁ ነበር።

24. ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁኝ፣እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣

25. ምክሬን ሁሉ ስለናቃችሁ፣ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣

26. እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤

27. መዓት እንደ ማዕበል ሲያናውጣችሁ፣መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠራርጋችሁ፣ሥቃይና ችግር ሲያጥለቀልቃችሁ አፌዝባችኋለሁ።

28. “በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፤ እኔ ግን አልመልስላቸውም፤አጥብቀው ይፈልጉኛል፤ ነገር ግን አያገኙኝም።

29. ዕውቀትን ስለ ጠሉ፣ እግዚአብሔርንም መፍራት ስላልመረጡ፣

30. ምክሬን ለመቀበል ስላልፈለጉ፣ዘለፋዬን ስለናቁ፣

31. የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፤የዕቅዳቸውንም ውጤት ይጠግባሉ።

32. ብስለት የሌላቸውን ስድነታቸው ይገድላቸዋል፤ተላሎችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፤

33. የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 1