ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ምሳሌ 1:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግራቸው ወደ ኀጢአት ይቸኵላል፤ደም ለማፍሰስም ፈጣኖች ናቸው።

17. ወፎች ፊት እያዩ ወጥመድ መዘርጋት፣ምንኛ ከንቱ ነው!

18. እነዚህ ሰዎች የሚያደቡት በገዛ ደማቸው ላይ ነው፤የሚሸምቁትም በራሳቸው ላይ ብቻ ነው።

19. ያላግባብ ለጥቅም የሚሯሯጡ ሁሉ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤የሕይወታቸው መጥፊያም ይኸው ነው።

20. ጥበብ በጐዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፤በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤

21. ዉካታ በበዛባቸው ጐዳናዎች ላይ ትጮኻለች፤በከተማዪቱም መግቢያ በር ላይ እንዲህ ትላለች፤

22. “እናንት ብስለት የሌላችሁ ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወዱታላችሁ?ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?

23. ዘለፋዬን ብትሰሙኝ ኖሮ፣ልቤን ባፈሰስሁላችሁ፣ሐሳቤንም ባሳወቅኋችሁ ነበር።

24. ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁኝ፣እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣

25. ምክሬን ሁሉ ስለናቃችሁ፣ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣

26. እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤

27. መዓት እንደ ማዕበል ሲያናውጣችሁ፣መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠራርጋችሁ፣ሥቃይና ችግር ሲያጥለቀልቃችሁ አፌዝባችኋለሁ።

28. “በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፤ እኔ ግን አልመልስላቸውም፤አጥብቀው ይፈልጉኛል፤ ነገር ግን አያገኙኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ምሳሌ 1