ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማሕልየ መሓልይ 5:4-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ውዴ እጁን በበሩ ቀዳዳ አሾለከ፤ልቤም ስለ እርሱ ይታወክ ጀመር።

5. ለውዴ ልከፍትለት ተነሣሁ፤በከርቤ ነጠብጣብ የራሱት እጆቼ፣በከርቤም ፈሳሽ የተነከሩት ጣቶቼ፣የመወርወሪያውን እጀታ ያዙ።

6. ለውዴ ከፈትሁለት፤ውዴ ግን አልነበረም፤ ሄዶአል፤በመሄዱም ልቤ ደነገጠ፤ፈለግሁት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም፤ጠራሁት፤ ነገር ግን አልመለሰልኝም።

7. የከተማዪቱም ጠባቂዎች፣በከተማዪቱ ውስጥ ሲዘዋወሩ አገኙኝ፤እነዚህ የቅጥሩ ጠባቂዎች፣ደበደቡኝ፤ አቈሰሉኝ፤ልብሴንም ገፈፉኝ።

8. እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤እማጠናችኋለሁ፤ውዴን ካገኛችሁት፣ምን ትሉት መሰላችሁ?በፍቅሩ መታመሜን ንገሩት።

9. አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ፤ውድሽ ከሌሎች እንዴት ቢበልጥ ነው?እስከዚህ የምትማጠኚንስ፣ውድሽ ከሌሎች እንዴት ቢበልጥ ነው?

10. ውዴ ፍልቅልቅና ደመ ግቡ ነው፤ከዐሥር ሺሆችም የሚልቅ ነው።

11. ራሱ የጠራ ወርቅ፣ጠጒሩ ዞማ፣እንደ ቊራም የጠቈረ ነው።

12. ዐይኖቹ፣በጅረት አጠገብ እንዳሉ ርግቦች፣በወተት የታጠቡ፣እንደ ዕንቊም ጒብ ጒብ ያሉ ናቸው።

13. ጒንጮቹ የሽቱ መዐዛ የሚያመጡ፣የቅመማ ቅመም መደቦችን ይመስላሉ፤ከንፈሮቹም ከርቤ እንደሚያንጠባጥቡ፣ውብ አበቦች ናቸው።

14. ክንዶቹ በዕንቊ ፈርጥ ያጌጠ፣የወርቅ ዘንግን ይመስላሉ፤ሰውነቱም በሰንፔር ፈርጥ ያጌጠ፣አምሮ የተሠራ የዝሆን ጥርስን ይመስላል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማሕልየ መሓልይ 5