ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሚክያስ 4 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእግዚአብሔር ተራራ

1. በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣ከተራሮች ልቆ ይታያል፤ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።

2. ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤በመንገዱ እንድንሄድ፣መንገዱን ያስተምረናል።”ሕግ ከጽዮን ይመጣል፤ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም።

3. እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ሰይፋቸውን ማረሻ፣ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል።አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።

4. እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።

5. አሕዛብ ሁሉ፣በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።

የእግዚአብሔር ዕቅድ

6. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“በዚያች ቀን ሽባውን እሰበስባለሁ፤ስደተኞችንና ለሐዘን ያደረግኋቸውን፣ወደ አንድ ቦታ አመጣለሁ።

7. የሽባዎችን ትሩፍ፣የተገፉትንም ብርቱ ሕዝብ አደርጋለሁ፤ከዚያች ቀን አንሥቶ እስከ ዘላለም፣ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።

8. አንተ የመንጋው መጠበቂያ ማማ ሆይ፤የጽዮን ሴት ልጅ ዐምባ ሆይ፤የቀድሞው ግዛትህ ይመለስልሃል፤የመንግሥትም ሥልጣን ለኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ይሆናል።”

9. አሁንስ እንደዚህ የምትጮኺው ለምንድን ነው?ንጉሥ የለሽምን?ምጥ እንደ ያዛት ሴት የተጨነቅሽው፣መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን?

10. የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፤ምጥ እንደ ያዛት ሴት ተጨነቂ፤አሁንስ ከከተማ ወጥተሽ፣በሜዳ ላይ መስፈር አለብሽና፤ወደ ባቢሎን ትሄጃለሽ፣በዚያ ከጠላት እጅ ትድኛለሽ፤ እግዚአብሔር በዚያ፣ከጠላቶችሽ ይታደግሻል።

11. አሁን ግን ብዙ አሕዛብ፣በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል፤እነርሱም፣ “የረከሰች ትሁን፤ዐይናችንም ጽዮንን መዘባበቻ አድርጎ ይያት” ይላሉ።

12. ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ አያውቁም፤በአውድማ ላይ እንደ ነዶየሚሰበስባቸውን፣የእርሱን ዕቅድ አያስተውሉም።

13. የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ተነሥተሽ አበራዪ፤የብረት ቀንድ እሰጥሻለሁና፤የናስ ሰኰና እሰጥሻለሁ፤አሕዛብንም ታደቂያቸዋለሽ።”በግፍ ያግበሰበሱትን ትርፍ ለእግዚአብሔር፣ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ ታቀርቢያለሽ።