ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሚልክያስ 3:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

6. “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።

7. ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዛቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።“እናንተ ግን፣ የምንመለሰው እንዴት ነው ትላላችሁ?”

8. “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን?” እናንተ ግን ትሰርቁኛላችሁ።“እናንተ ግን፣ ‘እንዴት እንሰርቅሃለን?’ ትላላችሁ።“ዐሥራትና መባ ትሰርቁኛላችሁ፤

9. እናንተም፣ መላው ሕዝባችሁም ስለምትሰርቁኝ የተረገማችሁ ናችሁ።

10. በቤቴ መብል እንዲኖር፣ እኔንም በዚህ እንድትፈትኑኝ ዐሥራቱን ሁሉ ወደ ጐተራ አስገቡ፤” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ “የሰማይን መስኮት የማልከፍትላችሁ፣ የተትረፈረፈ በረከትንም ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የማላፈስላችሁ ከሆነ ተመልከቱ።

11. ስለ እናንተ ተባዩን እገሥጻለሁ፤ አዝመራችሁን አይበላም፤ ዕርሻ ላይ ያለ የወይን ተክላችሁም ፍሬ አልባ አይሆንም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

12. “ከዚያም በኋላ የተድላ ምድር ስለምትሆኑ ሕዝቦች ሁሉ የተባረከ ሕዝብ ብለው ይጠሯችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

13. “በእኔ ላይ የድፍረት ቃል ተናግራችኋል” ይላል እግዚአብሔር።“እናንተ ግን፣ ‘በአንተ ላይ የተናገርነው ምንድን ነው?’ ትላላችሁ።

14. “እንዲህም ብላችኋል፤ ‘እግዚአብሔርን ማገልገል ከንቱ ነው፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ በማድረግና በእግዚአብሔር ጸባኦት ፊት ሐዘንተኞች ሆነን በመመላለስ ምን ተጠቀምን?

15. አሁን ግን ትዕቢተኞችን ቡሩካን እንላቸዋለን፤ ክፉ አድራጊዎች ይበለጽጋሉ፤ እግዚአብሔርን የሚፈታተኑትም ያመልጣሉ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሚልክያስ 3